group-telegram.com/Aflamagazine/14
Last Update:
አቦጮሮ
ከእኛ ሰፈር እንደ አቦጮሮ የቡሄ ትዝታ ሊኖረው የሚችል ሰው አይገኝም፡፡ በልጅነታችን የሆያሆዬ ቡድን አደራጅ ከመሆን ጀምሮ ሙልሙል እና ገንዘብ ያዥ ሆኖ በመስራት ፣ በአከባቢያችን ቡሄ ሲመጣ በሚደረገው የጅራፍ ግርፍያ እስከመሳተፍ ድረስ አገልግሏል፡፡ በጅራፍ ግርፊያው የእኛ ሰፈር ሁሌ እንዳሸነፈ የዘለቀውም በአቦጮሮ የጅራፍ ገመዳ እና አገራረፍ ጥበብ አመካኝነት ነው፡፡ የአቦጮሮ ጅራፍ ከፈረስ ጭራ እና ከቃጫ የተገመደ ጫፍ ሲኖረው ውስጡም የተደበቀ ቀጭንና ጠንካራ ሽቦ ይጨመርበታል፡፡ ለጅራፍ ግርፊያ የሚወጣ ማንኛውም ተጋራፊ ተበድሮም ይሁን ተለክቶ ያለውን ሰብስቦ ደራርቦ መልበስ ካልቻለ የአቦጮሮን የሽቦ ጅራፍ በየትኛውም አቅም መቋቋም እንደማይችል ግልፅ ነው፡፡ የፈለገውን ያህል ልብስ የደረበ ጎረምሳ በግርፊው የለበሰው እላዪ ለይ እስኪያልቅ ስለሚፋለም ትዕይንቱ ማራኪም አሳቃቂም ነበር፡፡ ከሁሉም ከሁሉም በአቦጮሮ የቡሄ ትዝታ ውስጥ የሚገኑት ግን ወ/ሮ አጋረደች እና ጋሽ ተምትሜ ናቸው፡፡ ወ/ሮ አጋረደች በፀባያቸው ሰው ማቅረብም ሆነ ከቤታቸው ማስገባት የማይጥማቸው ስለሆኑ አቦጮሮ እና ጓደኞቹንም በአንዱ ቡሄ ጉድ ሰርተዋቸዋል፡፡ እንደልማዳቸው ሆ ለማለት በሄዱበት የአሳማ ስጋ ቅንጣቢ እየቀለቡ ያሳደጉትን አንበሳ የሚያህል ተናካሽ ውሻ ለቀው ያልያዘውን አባሮ አፉ የገባውን አቦጮሮ ሱሪ ጎትቶ ከመሬት ካንከባለለው በኃላ ለማስለቀቅ ሲወራጭ የጆሮውን በጥርሱ ስለጎመደው አቦጮሮ እስካሁን በግማሽ ጆሮ ቀርቷል፡፡ ሆኖም ግን ከወይዘሮ አጋረደች በተለየ ጋሽ ተምትሜ በራፍ መድረስ የማይቻለው የቡሄ እና የእንቁጣጣሽ ቀን ብቻ ነው፡፡ሰበቡ ደግሞ ጋሽ ተምትሜ ልመና አጥብቀው በመጥላታቸው የእኛ በበአል እና በጭፈራ እያመካኙ ገንዘብና ሙልሙል መቀበል ስለማይጥማቸው ነው፡፡ ያም ሆኖ ልባቸው ቡቡና መንፈሳቸውም ደና ግጥም ወዳድ ስለሆነ ሁላችንም በዚም በዚያም ገብተን ተሸልመን መውጣታችን አይቀሬ ነው፡፡ እንደውም በዚህ አጋጣሚ ባለፈው ማለዳ ለይ ከጊቢያቸው በራፍ ለልመና የቆመች የጠዋት አዝማሪ (ላሊበላ)
"የዘንድሮ ነገር ቁርጡም አልታወቀ ፣
ወሬ በመጠየቅ ልባችን ወለቀ፡፡ " ብላ በመግጠሟ ሀምሳ ብር ሰጥተው አሰናብተዋታል፡፡ አቦጮሮና ጓደኞቹም ሆያ ሆዬ ለመጨፈር ቤታቸው በሄዱ ቁጥር ጋሽ ተምትምን የሚያሞግስ ግጥም ስለሚያወርዱ ተሸልመው መላካቸው የታወቀ ነው፡፡ የነ አቦጮሮን ድምፅ ከሩቅ ሲሰሙ "በይ ማነሽ ነይ በሬን ገጥመሽ ዝጊልኝ ፍጠኚ!" እያሉ የቆዩት ተምትሜ ሆ ባዮቹ ደርሰው.....
"የኔማ ጌታ ጌታ ጠንበለል ፣
ዝናቡ መጣ ወዴት ልጠለል፡፡" ማለት ሲጀምሩ "ድሮስ እኔ ተምትሜ እየዞርክ ቂጣ ልቀም ብዬሃለው ነይ ክፈቺ አንቺ!" ይሉና የቤት አገልጋያቸውን ያዛሉ፡፡ አቦጮሮም ስሜታቸውን እያነበበ ......
"የኔማ ተምትም የሰጠኝ ሙክት ፣
ግንባረ ቦቃ ባለምልክት፡፡" ይላል ይሄኔ ከሙልሙሉ አንድ ሁለቱን ከብሩም እጃቸው የገባውን አድርገው ያሰናብታሉ፡፡ ታድያ ከቆዳ የተሰራውን የሙልሙል መያዣ ከረጢት የሚያነግተው አቦጮሮ ከየቤቱ የሰበሰቡትን ሙልሙል በየአይነቱ ተሸክሞ መጎዝ ብቻ ስለማይሆንለት ወደኃላ ቀረት እያለ ካማረው ለይ ስለሚገምጥ ከፊት የቀደሙት ጓደኞቹ ፈጥኖ እንዲራመድ ለመንገር ስሙን ሲጠሩ በአፉ የሚወትፈው ዳቦ ድምፁን እያፈነው ነበር "አቤት" የሚለው፡፡እንዲሁ እንደልማዱም በአንዱ ቡሄ ከአንዱ ቤት ለመግባት ሲጣደፉ ከየቤቱ ከተገኘው ሙልሙል እየቆረሰ የሚበላው አቦጮሮ ከመጠን በላይ ሆዱ ተነፍቶ ስለነበር መራመድ አቅቶት ሲወላገድ ከጋሽ ተምትሜ ቤት ፊት ለፊት መንገዱ ተቦርቡሮ ጎርፍና ለብዙ ወራት የተጠራቀመ ቆሻሻ ከሞሉት ጉድጓድ ተሻገርኩ ብሎ ስለወደቀ እከክ ይዞት ሁላችንም ከአጠገቡ እንዳንደርስ ማስጠንቀቂያ ይሰጠን ነበር፡፡ ይኸው አሁንም ቢሆን ቆሻሻ ውሃ ውስጥ በመውደቁ የያዘው እከክ ለረጅም ጊዜ ከአካሉ ጋር በመቆየቱ ተሽሎት እንኳን ቆዳው ተዥጎርጉሮ ቀርቷል፡፡ አቦጮሮና ቡሄ በሰፈራችን ታሪክ ካለመላቀቃቸው የተነሳ ይኸው ዛሬ እንኳን አዳዲሶቹ የሰፈራችን ሆያ ሆዬ ተጨዋቾች ከአቦጮሮ በራፍ ቆመው በራሳቸው ግጥም
"ሆያ ሆዬ ጉዴ ፣
ጋሽ ቡራቡሬ ጆሮ ጎማዴ ፣
ሙልሙል ሙልሙል ይላል ሆዴ፡፡" እያሉ በነገር ሲወርፉት ውለዋል፡፡
✍እፀገነት መልካሙ
መልካም የቡሄ በዓል!!!
@Aflamagazine
@Aflamagazine
BY አፍላ መፅሔት
Warning: Undefined variable $i in /var/www/group-telegram/post.php on line 260
Share with your friend now:
group-telegram.com/Aflamagazine/14