group-telegram.com/tikvahethiopia/94828
Last Update:
#የአርሶአደሮችድምጽ
🔴 “ ለሦስት ዓመታት ምንም የካሳ ክፍያ አልተከፈለንም፡፡ የምንመገበው አጥተን ለልመና ተዳርገናል” - አርሶ አደሮች
➡️ “ ክፍያዎቹን በተገቢው በሚፈለገው አግባብ እየከፈልን አይደለም ” - የአማራ ክልል መንገዶች ቢሮ
በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ ከቸና እስከ መካነ ኢየሱስ ከተማ ባለው የመንገድ ፕሮጀክት መሬት የተወሰደባቸው ወደ 40 አርሶ አደሮች ለ3 ዓመታት የካሳ ባለመከፈሉ ለልመና መዳረጋቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡
አርሶ አደሮቹ ስለቅሬታቸው ምን አሉ?
“ ከቸና እስከ መካነ ኢየሱስ ከተማ ድረስ ባለው ፕሮጀክት ለተወሰደው መሬት 2014 ዓ/ም የካሳ ክፍያ ብናውቅም 40 አርሶ አደሮች ለ3 ዓመታት ካሳ አልተከፈለም፡፡
በአሰራሩ መሰረት የካሳ ክፍያ እንደወቅቱ ሁኔታ እየታዬ በየስድስት ወሩ ማሻሻያ ይደረግበታል ክፍያ ሳይፈጸም ከቆዬ። የኛ ግን ለ3 ዓመት ማሻሻያ አልተደረገበትም፡፡
ከዓመታት በፊት የተገመተው ካሳ አሁንም ባለበት ነው። ከ3 ዓመታት በፊት የነበረው የገንዘብ ዋጋ ከአሁኑ ጋር ሲነጻጸር ሰፊ ልዩነት አለው። ያም ሆኖ ግን ከዓመታት በፊት የነበረው ካሳም እየተከፈለን አይደለም፡፡
የመካነ ኢየሱስ ከተማ ነዋሪም ቤቱን ሽጦ እንዳይመገብ መስመር ዳር ሊፈርስ ምልክት ስለተደረገበት መሸጥ አይቻልም፡፡ የገጠሩ አርሶ አደርም የተወሰደብን መሬት የአትክልት ማምረቻ ጭምር ማሳ ነው፡፡
አርሶ አደሩ እስከ 3 ማሳ ነበረው በግራና ቀኝ መንገድ ፕሮጀክቱ የደረደበት፡፡ አርሶ አደሩ ወይ አርሶ አልተጠቀመ ወይ የካሳ ክፍያ አላገኘ፡፡ አትክልቱ እንኳ አድጎ ጥቅም እንዳይሰጥ በለጋው ተቀጭቷል ” ብለዋል።
በ2014 ዓ/ም በነበረው የካሳ ተመን መሰረት ከ200 ሺሕ እስከ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የተገመተላቸው አርሶ አደሮች እንዳሉ ገልጸው፣ በአሁኑ የገንዘብ የመግዛት አቅም ዋጋ ተተምኖ በቶሎ ካሳው እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ፣ ለምን የአርሶ አደሮቹ ካሳ በወቅቱ አልተከፈለም፣ መቼስ ይከፈላለቸዋል? ሲል የአማራ ክልል መንገዶች ባለስልጣንን ጠይቋል።
የአማራ ክልል መንገዶች ቢሮ ምን መሰለ?
“ የወሰን ማስከበር ክፍያዎች በመንግስት በጀት ከምንከፍላቸው ክፍያዎች አንዱ ነው። ግን ክፍያዎቹን በተገቢው በሚፈለገው አግባብ እየከፈልን አይደለም።
ይሄ ደግሞ የተፈጠረው ለመስሪያ ቤታችን ከመንግስት በሚለቀቀው በጀት ጋር ተያይዞ እየገጠመን ባለው የበጀት ችግር ነው።
ይሄን ችግር እናውቀዋለን። ለመፍታት እየታገልን ያለነው ነው። ስለዚህ የበጀት ችግሩ እንደተፈታልን፣ መፈታት ብቻም ሳይሆን እንደተቃለልን ቀሪ ክፍያዎችን ባለው ፕራዮሪቱ ኦርደር መሠረት እንከፍላለን ” ብሏል።
(ጉዳዩን እስከመጨረሻው የምንከታተለው ይሆናል)
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia