group-telegram.com/yabsiratesfaye/127
Last Update:
🛑 ፃማ 🛑
ክፍል አስራ አንድ
በእሷ የመጣ ማንንም ቢሆን አይምሩም። ብቸኛ ልጃቸው ናትና። እንደ ዐይናቸው ብሌን ይሳሱላታል። ታዲያ በዚህ አይነት አስተዳደግ ያደገችው ትዝታ ፈልጋ ልታገኘው ያልቻለችው አንድ ነገር አልአዛርን ብቻ ቢሆን ምን ያስገርማል? ለእሷ የተመኘችሁን ማጣት ትልቅ ሽንፈት ነው። ሽንፈትን ደግሞ በፀጋ የሚቀበል ጭንቅላት የላትም። በፍፁም ላጣው አልችልም ብላ ለራሷ ደምድማለች።
በቅርቡ በመካከላቸው ግጭት ስለተፈጠረ ለጥቂት ቀናት ታግሳ ከእሱ ላለመገናኘት ወስናለችና ወደ ቤቱ ዝር አላለችም። ወደ ሱቁም ቢሆን አልሄደችም። ዐይኑን ካየች ሶስት ቀናት ቢያልፋትም ቢያንስ አንድ ሳምንት በትዕግስት ለማሳለፍ ራሷን አጠነከረች።
አልአዛር የትዝታ መጥፋት ቢያስገርመውም አጋጣሚው አስደስቶታል። እስከመጨረሻው ባያገኛት ምርጫው ነው። አልአዛር ትዝታን ከብሌን ጋር ሲያነፃፅር ልዩነታቸው የሰማይና የምድር ሆነበት። ብሌን ነገሮችን አጢና አውጥታና አውርዳ ነው የምታከናውናቸው። በዚህ በጭንቅ ጊዜ ላይ ሆና ራሱ ራሷን እንደጠበቀች ነው። ትዝታ ግን! አለ በሆዱ ትዝታ ግን ደገመው "ከራሷ ውጪ ለሌላው የማታስብ ስግብግብ ናት። ምቾቷ ይጠበቅ እንጂ ማንኛውም ሰው ለእሷ ፍላጎት ቢሰቃይ ግድም አይሰጣት። በአንድ ወቅት ከእንደዚች አይነት ሴት ጋር የፍቅርን ግንኙነት መመስረቱ አሁን ድረስ ያስገርመዋል።
በሀሳብ ብዙ እንደተጓዘ የውጪው በር ተንኳኳ። ብሌን የምትገባበት ጠፍቷት በፍርሀት ትንቀጠቀጥ ጀመር። አልአዛር ከትላንት በስቲያ ከሁለት ሳምንት በኃላ መጣለው ብሎት የሄደው ናትናኤል ዛሬ ሊመለስ እንደማይችል ያውቃል። ታዲያ ማን ሊሆን ይችላል? ራሱን በራሱ ጠየቀ። ድጋሜ በሩ ተንኳኳ። ትዝታ ብትሆንስ የሚለው ግምት ሲታሰበው ሊፈጠር የሚችለው ችግር ገና ካሁኑ ዘገነነው።
ፈራ ተባ እያለ ወደ በሩ አመራ። ለነገሩ በሩን ሲያንኳኳ የነበረው ሱቁ ውስጥ አብሮት የሚያሻሽጠው ታዳጊው አብይ ነበር። ያለቀ እቃ መግዣ ገንዘብ ሊወስድ ነበር አመጣጡ። የአልአዛር ልብ መለስ አለች። ገንዘቡን ከሰጠው በኃላ በሩን ጥርቅም አድርጎ ዘጋው። ቢሆንም ብሌንን ማነች ብሎ ለትዝታ እንደሚናገር ጨነቀው። በኃላ በኃላ አንድ ሀሳብ መጣለት። አብሮት የሚኖረው ናትናኤል!
ብሌን የናትናኤል እጮኛ ናት ብሎ ለትዝታ ሊዋሻት ይችላል። መቼስ ከናትናኤል ፀባይ አንፃር የማይታመን ነገር ነው። እንደምንም ብሎ ግን ማሳመን አያቅተውም። ዋናው ጭንቅ ግን ናትናኤል በሌለበት እሷ እዚህ ምን ትሰራለች የሚለው ጥያቄ ነው። ለዚህ የሚሆን ውሸት መፍጠር ከበደው። ሌላው የረሳው ጉዳይ ይሄንን ዘዴውን ለብሌንም ሆነ ለናትናኤል አልነገራቸውም። የልብ ጓደኛው ናትናኤል ትንሽ ባያንገራግርም እሺ እንደሚለው አይጠራጠርም። ግን ብሌንስ? ሌላ ጥያቄው ነበር። አሁኑኑ ሊነግራት ይገባል። ምን አልባት ትዝታ ዛሬ ልትመጣ ትችላለች።
በረንዳው ላይ ቆሞ ይሄንን ነገር ሲያውጠነጥን የብሌንን ከጀርባው መቆም አላስተዋለም። ማን ነበር? አለች ብሌን! ስጋቷ ከፋቷ ላይ ይነበባል። አይ የሚያስጨንቅ አይደለም። ሱቁ ውስጥ የሚሰራው ልጅ ነው። አለ ፈገግ እንደማለት ብሎ። እንዴት ብሎ እንደሚነግራት እያሰበ ነው። ኧ .... ብሌን ብሎ ጀመረ። ራስሽን ከአደጋ ለመጠበቅ ስትዪ አንድ ነገር ልታደርጊ ይገባል አለ ጨርሶ ለመናገር ድፍረት አጥቶ።
ምን? ምን ማድረግ ይገባኛል? አለችው ግራ በተጋባ ስሜት። አንድ አብሮኝ የሚኖር ጓደኛ አለኝ። ለታማኝነቱ ምንም ጥርጥር የለኝም። ለጊዜው አብሮኝ አይገኝም። ነገር ግን ከሁለት ሳምንት በኃላ ይመጣል። ወደ እዚህ ቤት ለሚመጣ ሰው ሁሉ የእሱ እጮኛ እንደሆንሽ እንድትናገሪ እፈልጋለው። አለ የልቡን ተንፍሶ። የእሷን ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ነው። የማታውቀው ሰው እጮኛ ነኝ ብሎ የመናገሩ ጥቅም ባይገባትም አንገቷን በእሺታ ነቀነቀች።
✍️✍️✍️✍️ ይቀጥላል
@yabsiratesfaye ለወዳጅ ለዘመዶ ያጋሩ
BY አርያም - ARYAM
Warning: Undefined variable $i in /var/www/group-telegram/post.php on line 260
Share with your friend now:
group-telegram.com/yabsiratesfaye/127